
Feta Daily News
ኢትዮጵያ ከሩሲያ የገዛቻቸው ተዋጊ ጄቶችና የአየር መከላከያ ሥርዓቶች በግብፅ ሥጋት መፍጠራቸው ተዘገበ
ኢትዮጵያ 12 የሱ35 ተዋጊ ጄቶችን መረከቧና የኤስ-400 የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን ለመታጠቅ መዘጋጀቷ በአፍሪካ ቀንድ የኃይል ሚዛን ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩን ኢንዲፔንደንት አረቢያ በዛሬው ዘገባ አመልክቷል።
የካይሮ ዲፕሎማሲያዊ ምንጮች፤ ይህ የጦር መሣሪያ ዝግጅት የግብፅን ወታደራዊ የበላይነት አይቀይረውም ሲሉ ተከላክለው፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አካባቢ የባሕር በር ለማግኘትና ቀጠናዊ ተፅዕኖዋን ለማሳደግ በምታደርገው ጥረት ውስጥ ስልታዊ ጥቅሟን ለማስከበር ልትጠቀምበት ትችላለች የሚል ሥጋት በግብፅ ዘንድ መፈጠሩን አልሸሸጉም።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግዢው የሀገሪቱን የመከላከል አቅም ለማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የታለመ መሆኑን ማስታወቁ አይዘነጋም።
የእስራኤል ምርጫ ዕልባት አላገኘም፤ ተቃዋሚዎች ጋዲ አይዘንኮትን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲያጩ ኔታንያሁ የዓረብ ፓርቲዎችን ያገለለ ጥምረት ጠየቁ
በእስራኤል ምርጫ የትኛውም ወገን የላቀ መቀመጫ ባለማግኘቱ የፖለቲካ ቀውስ የተፈጠረ ሲሆን፣ የተቃዋሚው ጎራ ጋዲ አይዘንኮት ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ በጋራ ለመደገፍ ተስማምተዋል።
በአንጻሩ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ፓርቲያቸው ከፍተኛ መቀመጫ ማግኘቱን በመጥቀስ ጥምር መንግሥቱን እሳቸው ሊመሩት እንደሚገባ ገልጸው፣ ሪኮርድ 19 መቀመጫ ያሸነፉትን የዓረብ ፓርቲዎች ያገለለ ሰፊ ብሔራዊ መንግሥት ለመመሥረት ጥሪ አቅርበዋል።
የተቃዋሚው ጎራ 48 መቀመጫ እና የኔታንያሁ ወገን 53 መቀመጫ ስላላቸው፣ ወሳኝ የሆኑትን የዓረብ ፓርቲዎች በጥምረት ውስጥ ስለማካተት በተቃዋሚዎች ዘንድ የሃሳብ ልዩነት ያለ ሲሆን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መንግሥት የሚመሠርት ዕጩ ለመሰየም ከነገ ጀምሮ ከፓርቲዎች ጋር ምክክር ይጀምራሉ።
ምንጭ፦ ፍራንስ 24
https://youtu.be/_UbgdVzphpY?si=pUWo_Dvt_LEPEBb3
ግብፅ እና ሱዳን የኢትዮጵያን ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም መብት የሚጋፋ ማሳሰቢያ ሰጡ
ግብፅ እና ሱዳን በካይሮ ባካሄዱት ስብሰባ የአገሪቱን ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም መብት የሚጋፋ መግለጫ አውጥተዋል። ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገራት የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚገድበውንና ሌሎችን የአባይ ተፋሰስ አገራትን ያገለለውን የ1959ኙን አግላይ የውኃ ክፍፍል ስምምነት በድጋሚ ለማንጸባረቅ የሞከሩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የወደፊት የልማት እርምጃዎች በአንድ ወገን ውሳኔ የመመደብ አካሄድ ተከታትለዋል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ማናቸውም ዓይነት የአባይ ውኃ ድርድር ሁሉንም የተፋሰሱ አገራት ያካተተና ፍትሐዊ መሆን እንዳለበት በተደጋጋሚ የገለጸች ሲሆን፣ የግብፅና ሱዳን የትናንቱ የካይሮ ስብሰባ ግን ጉዳዩን በሁለቱ አገራት መካከል ብቻ ለመገደብ ያለመ ነው።
ዚህም በተጨማሪ ሁለቱ አገራት በቀይ ባሕር አካባቢ ያለውን ወታደራዊና የባሕር ላይ እንቅስቃሴ በማውገዝ፤ ኢትዮጵያ ቀጠናዊ ተደራሽነቷንና ብሔራዊ ደኅንነቷን ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት ዲፕሎማሲያዊ እንቅፋት ለመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል።
የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች የኢራንን የዓሣ ማጥመጃ መርከብ ከተሳፋሪዎቿ ጋር አገቱ
የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች 23 ሰዎችን ያጫነች የኢራን የዓሣ ማጥመጃ መርከብን በቁጥጥራቸው ሥር ማዋላቸውን የሕንድ ውቅያኖስ የባሕር ደኅንነት ማዕከል አስታውቋል። አዚኒ የተሰኘችው ይህች መርከብ የታገተችው በሰሜን ምስራቅ ሶማሊያ ፑንትላንድ የባሕር ዳርቻ ሲሆን፣ በመርከቧ ላይ 21 የኢራን የሠራተኞች አባላት እና ሁለት የሶማሊያ የደኅንነት ጠባቂዎች ይገኙባታል።
ታጣቂዎቹ መርከቧን በዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች መተላለፊያ መስመር ላይ ሌሎች የጭነት መርከቦችን ለማጥቃት እንደ የጦር ሰፈር ሊጠቀሙባት ይችላሉ የሚል ከፍተኛ ሥጋት ተፈጥሯል።
ይህ አዲስ ጥቃት በኤደን ባሕረ ሰላጤ እና በምዕራብ ሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እያገረሸ መምጣቱን የሚያመለክት ሌላው ማሳያ ሆኗል። የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ኃይል ግብረኃይል በጉዳዩ ላይ ምርመራ እያደረገ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚያልፉ መርከቦች በሙሉ ጥብቅ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
11 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ኢትዮጵያ ከልማት አጋሮች እየፈለገች መሆኑ ተገለጸ
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2035 መላውን ህዝብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ያቀደችውን የ18 ቢሊዮን ዶላር ብሄራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን መርሃ ግብር ለመደገፍ፣ ከዓለም ባንክ እና ከሌሎች የልማት አጋሮች የ11 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እየፈለገች መሆኑን ቢኤንኢ ኢንተሊኒውስ የተባለው የዜና ወኪል የካፒታል ጋዜጣን መረጃ ጠቅሶ ዘግቧል።
ይህ እቅድ እስከ 2035 ድረስ 32.5 ሚሊዮን ለሚሆኑ አባወራዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማድረስ ያለመ ሲሆን፣ አብዛኞቹ በሀገራዊ የኃይል መረብ እንዲሁም 4.4 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከዋናው መረብ ውጭ በሆኑ እንደ ሶላር ባሉ አማራጮች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ሀገሪቱ ከፍተኛ የኃይል ማመንጨት አቅም ቢኖራትም የኃይል ማከፋፈያ መሠረተ ልማት እና የመጨረሻ መስመር ዝርጋታ እጥረት ዋና ማነቆ በመሆኑ፣ መንግስት የኤሌክትሪክ ተደራሽነቱን ለማስፋፋት ከዓለም አቀፍ ተቋማት የእርዳታና የብድር አጋርነትን ለማጠናከር እና የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በንቃት እየሰራ ይገኛል ነው የተባለው።
https://youtu.be/iAdpBJXU_gw?si=bvK6hmG1cu2Q4WQW
ሱዳን በድሮን ጥቃቶች ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ለአፍሪካ ህብረት አቤቱታ አቀረበች
ሱዳን በግዛቷ በሚገኙ የሲቪል ተቋማት እና የኤሌክትሪክ ጣቢያዎች ላይ ለተሰነዘሩት የድሮን ጥቃቶች የኢትዮጵያ ግዛት ጥቅም ላይ ውሏል በማለት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እና ለአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት የቅሬታ አቤቱታ ማቅረቧን አስታውቃለች።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፈጣን ደጋፊ ኃይሎች የተባለው ታጣቂ ቡድን የኢትዮጵያን ግዛት በመጠቀም ጥቃቱን መፈጸሙን የሚያሳዩ ሰነዶችን ማቅረቡን የገለጸ ሲሆን፣ ድርጊቱን የሉዓላዊነት መጣስ እና የጠላትነት ተግባር በማለት ኮንኖታል።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ለታጣቂው ቡድን ድጋፍ እንደማታደርግና የሱዳንን ሉዓላዊነት እንደምታከብር በመግለጽ የቀረቡባትን ክሶች ያስተባበለች መሆኑን አናዶሉ በዘገባው አመልክቷል።
ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለመገንባት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን እየገመገመች መሆኑን ሮሳቶም አስታወቀ
የሩሲያ መንግስታዊ የኒውክሌር ኢነርጂ ኮርፖሬሽን (ሮሳቶም) ዋና ስራ አስፈፃሚ አሌክሲ ሊካቼቭ እንደገለጹት፣ ተቋማቸው ከኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ጋና እና ግብፅ ጋር ታላላቅ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ ውይይቶችን እያደረገ ይገኛል።
በሞስኮ በተካሄደው 3ኛው የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ይፋ እንደተደረገው፣ ኢትዮጵያ ከሮሳቶም ጋር ቀደም ሲል የተፈራረመችውን የትብብር ፍኖተ ካርታ መነሻ በማድረግ የማመንጫ ጣቢያው ሊገነባባቸው የሚችሉ እምቅ ቦታዎችን የመለየት ስራ እየተከናወነ ሲሆን፣ በቅርቡም የመጀመሪያ ደረጃ የምህንድስና ጥናቶች ይጀመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሆኖም ፕሮጀክቶቹ በአሁኑ ወቅት በቅድመ ዝግጅትና በውይይት ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው እስካሁን የመጨረሻ የገንዘብ ድጋፍ ወይም የኮንስትራክሽን ስምምነት አልተፈረመም።